በቦምባይ አውሮፕላን መጸዳጃ ቤት ውስጥ 12 ኪሎ ግራም ወርቅ ደብቀዋል የተባሉ ሶስት ኢትዮጵያውያን መያዛቸው ተሰማ
በህንድ ሙምባይ የሚገኘው የገቢዎች ደህንነት መመሪያ (DRI) ባለስልጣናት ከአዲስ አበባ በተነሳ አውሮፕላን መጸዳጃ ቤት ውስጥ በግምት 2.1 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ 12 ኪሎ ግራም ወርቅ በድብቅ ይዘው የገቡ ሶስት የኢትዮጵያ ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታወቁ። ተጠርጣሪዎቹ አህመድ አብዱራህማን ፣ መሐመድ አብዱራህማን እና ጀሚል ኑሪ መሐመድ የተባሉ ሲሆን ባለፈው ሀሙስ ምሽት አውሮፕላኑ ሙምባይ እንዳረፈ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲል ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ዘግቧል። ባለስልጣናቱ ቀደም ብለው ባገኙት ጥቆማ መሰረት ፍተሻ ባካሄዱበት ወቅት በተጠርጣሪዎቹ የእጅ ቦርሳ ውስጥ የአውሮፕላኑን ግድግዳዎች መፍቻ መሳሪያዎችን አግኝተዋል። በተደረገባቸው ጥብቅ ምርመራ፣ ወርቁን በአውሮፕላኑ የኋላ መጸዳጃ ቤት ግድግዳዎች ውስጥ ለመደበቅና በኋላም በአየር መንገድ የጽዳት ሰራተኞች አማካይነት ለማስወጣት ማቀዳቸውን አምነዋል። ፍተሻውን ተከተሎም 6 የወርቅ ባር ብረቶች ተገኝተዋል። ተጠርጣሪዎቹ የህንድን ህግ አያውቁም ቢሉም፣ ፍርድ ቤት በቁጥጥር ስር ውለው እንዲቆዩ ብይን አስተላልፎባቸዋል።