ጄነራል ታደሰ ወረደ ወዴት ተሰወሩ?
የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በመቀሌ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መሰወራቸው ተሰማ። እስከ ማክሰኞ ጠዋት ድረስ መኖሪያ ቤታቸው በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቅና በጥበቃ ተሽከርካሪዎች የተከበበ የነበረ ቢሆንም፣ ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ ግን አብረዋቸው የነበሩ ጥበቃዎችና ሰራተኞች ከአካባቢው ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል። ጄነራሉ ከጥቂት ቀናት በፊት ከአሜሪካው አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጋር እንዳይገናኙ በትግራይ ጸጥታ ቢሮ ተከልክለው እንደነበርና ቤተሰቦቻቸውም ስለ ደህንነታቸው ስጋት አድሮባቸው እንደነበር ይታወቃል። ጄነራል ታደሰ ወረደ በፌደራል መንግሥት ዳግም በተሾሙ በጥቂት ቀናት ውስጥ በሕወሓት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው የሚታወስ ነው። ከኃላፊነታቸው ከመነሳታቸው በፊትም ጊዜያዊ አስተዳደሩን በኃይል ለመገልበጥ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ክልሉን ወደ አዲስ ጦርነት እንደሚያስገባ አስጠንቅቀው ነበር። በአሁኑ ወቅት በሕወሓት እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው የፖለቲካ ውጥረት በጨመረበት ሁኔታ፣ የጄነራሉ ከአካባቢው መሰወር በትግራይ ክልል አዲስ የጸጥታ ስጋት ደቅኗል።