← All news
News Jul 23, 2026 · 47d ago

በወላይታ ሶዶ ከተማ ፌስታል ሲጠቀሙ በተገኙ 130 አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወሰደ

በወላይታ ሶዶ ከተማ በህግ የተከለከለውን ፌስታል ሲጠቀሙ በተገኙ 130 ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን የከተማው የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ጽ/ቤት አስታውቋል።እርምጃው በአብዛኛው በሱቆችና በንግድ ተቋማት ላይ የተወሰደ ሲሆን ከየካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው ክትትል የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል።   የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ጴጥሮስ ለማ ለብስራት ሬዲዮ እንደገለጹት የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1387/2017ን በመተላለፍ ፌስታል በመያዝ እና ለንግድ አገልግሎት ጥቅም ላይ ሲያውሉ በተገኙ 130 አካላት ላይ በህጉ መሠረት እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።በቅርቡ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንድ ነጋዴ 17 ኩንታል ማዳበሪያ ይዞ በመገኘቱ የተወረሰበት ሲሆን በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ጨምር እንዲቀጣ ተደርጓል።   በመሆኑም ግለሰቦችና ተቋማት ፌስታል መጠቀም በህግ የተከለከለ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ህጉን ሊያከብሩ ይገባል ሲሉ አቶ ጴጥሮስ ለማ  ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።በአዋጁ መሰረት ፌስታል ይዞ የተገኘ ግለሰብ  በ2 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል።እንዲሁም በተቋም ደረጃ ፌስታል ያከማቸ፣ የሸጠ ወይም ለንግድ ዓላማ እንደ እቃ መያዣ ያቀረበ ተቋም እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እና ባለንብረቶችም  እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጡ በአዋጁ ተጠቅሷል ።