አሜሪካ በኢራን ላይ የምታካሂደውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች
አሜሪካ ለ11ኛ ተከታታይ ምሽት በኢራን ላይ የአየር ጥቃት የሰነዘረች ሲሆን፥ቴህራን በበኩሏ ዋሽንግተን በኑክሌር ተቋማቷ ላይ ከሚሰነዘር ጥቃት እንድትቆጠብ አጥብቃ አስጠንቅቃለች። የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጸው፥የተሰነዘረው የጥቃት ማዕበል “ኢራን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ የምታደርሰውን ዛቻ የመቀነስ” አላማ ያለው ነው። የኢራን መንግስት መገናኛ ብዙሃን በዋና ከተማዋ ቴህራን የአየር መከላከያ ስርአቶች መስራታቸውን ዘግበዋል። በተጨማሪም በታብሪዝ፣ ቻባሃር፣ ኮናራክ እና የሀገሪቱ ብቸኛ የኑክሌር ሀይል ማመንጫ በሚገኝበት ቡሼህር ከተሞች የፍንዳታ ድምፆች ተሰምተዋል። ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በናታንዝ አቅራቢያ የሚገኘውን የመሬት ውስጥ የኑክሌር ተቋም በቅርቡ እንደምትመታ ከተናገሩ በኋላ፤ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ያስጠነቀቀችው ኢራን በአሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ወዳጆቿ ላይ አጸፋዊ ጥቃት እንደምትሰነዝር ገልጻለች።