የወረቀት ሳሙናን ለገበያ ያቀረበችው የባቲ ከተማዋ ወጣት
ባቲ፣ ኢትዮጵያ — አብዛኞቻችን ሳሙናን በደረቅ (በቁራጭ)፣ በዱቄት ወይም በፈሳሽ መልክ ብቻ አውቀን ለለመድነው አጠቃቀም፣ የባቲ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ኢክራም ሙሐመድ አዲስና ምቹ አማራጭ ይዛ ብቅ ብላለች። ወጣቷ ከአካባቢዋ ችግሮች በመነሳት ለእጅ መታጠቢያ የሚሆን «የወረቀት ሳሙና» በመፍጠር የብዙዎችን ትኩረት ስባለች። ኢክራም ለዚህ የፈጠራ ሥራዋ መነሻ የሆነውን አጋጣሚ ስታብራራ፤ በተለያዩ ቦታዎች ለስራና ለጉዞ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እጅ ለመታጠብ የሚሆን ሳሙና ማጣት የተለመደ ፈተና በመሆኑ፣ ይህንን ክፍተት የሚሞላ መፍትሔ ለመፈለግ መነሳቷን ትናገራለች። ይህ የወረቀት ሳሙና ከባህላዊ የሳሙና አይነቶች የሚለዩት በርካታ አዎንታዊ ጎኖች አሉት፦ * ቀደም ሲል ከምናውቃቸውና ለተላላፊ በሽታዎች ሊያጋልጡ ከሚችሉ የጋራ መጠቀሚያ ሳሙናዎች በተለየ፣ እያንዳንዱ ሰው ለብቻው በግል ለመጠቀም በሚመች መልኩ የተዘጋጀ ነው። * በቦታ፣ በሁኔታዎችና በቦርሳ ጥበት ሳይገደቡ በየትኛውም ስፍራ ይዞ ለመንቀሳቀስ እና ለመጠቀም አጅግ ምቹ ነው። * ከአንዱ ጥቅል ላይ አንድ ቀጭን ወረቀት በመለየት በእጅ ላይ አድርጎ በጥቂት ውሃ በማሸት ብቻ በቀላሉ መጠቀም ይቻላል። ምርቱን ለማዘጋጀት በአካባቢዋ በቀላሉ የሚገኙ ጥሬ እቃዎችን የተጠቀመች ሲሆን፣ የእጅ ቆዳን በማይጎዳ መልኩ የኬሚካል ውህዶችን በራሷ በማቀናጀት ለወረቀት ሳሙናው የሚፈለገውን ቅርጽ አስይዛዋለች። ለዚህ ስኬቷም የአባቷ እገዛና ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበረ ትገልጻለች። ምርቷን በአካባቢዋ መጠሪያ «ገንደዳዩ» በሚል ስያሜ ሰይማ ወደ ገበያ ያቀረበችው ወጣት ኢክራም፤ በተለያዩ ባዛሮች ላይ በማሳተፍ ከተጠቃሚዎች እጅግ አዎንታዊ እና አበረታች ግብረ-መልስ ማግኘቷን ተናግራለች። በቀጣይም የዚሁን የወረቀት ሳሙና ጥራትና መጠን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር በስፋት ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ጠንክራ እየሰራች እንደሆነና የወደፊት አላማዋም ምርቱን ማስፋፋት እንደሆነ ገልጻለች። Via አሚኮ